Divine Liturgy Service Hours: Saturday @ 5:00 am – 8:00 am | Sunday @ 4:00 am – 7:00 am

የስሙትርጉም

«መጻጒዕ» የሚለው ቃል የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም «በሽተኛ» ወይም «ድውይ» ማለት ነው ። በዚህም ሳምንት ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው (በምድር በነበረበት ወቅት) ካደረጋቸው ታላላቅ ተአምራት መካከል አንዱ የሆነውንና ለ፴፰ (ሠላሳ ስምንት) ዓመታት ያህል በአልጋ ቁራኝነት ተይዞ የነበረውን በሽተኛ የፈወሰበትን ድንቅ ተአምር እናስባለን ።
ቅዱስ ያሬድም በደዌ የተያዙ ወገኖች ሁሉን ቻይ የሆነውን ጌታ ተስፋ ያደርጉ ዘንድና በክርስቶስ አማካኝነት ከደዌ የዳኑትን ለማሰብ ይህንን ሳምንት «መጻጒዕ» ብሎ ሰይሞታል

ቤተሳይዳ 

በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፭ (አምስት) ላይ እንደተገለጸው፣ በኢየሩሳሌም በምትገኘው «ቤተ ሳይዳ» (የምሕረት ቤት) አቅራቢያ አምስት የመመላለሻ ስፍራዎች ያሏት አንዲት መጠመቂያ ነበረች ። በዚህች ስፍራ በርካታ ሕሙማን (ዕውራን፣ አንካሶችና ሰውነታቸው የሰለለ) ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር ።

የውኃው መናወጥ የሚከሰተው የእግዚአብሔር መልአክ በየጊዜው ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ሲያናውጠው ነበር ። ውኃው በተናወጠ ጊዜም ቀድሞ የገባ አንድ በሽተኛ ብቻ ይፈወስ ነበር ።

የጌታርኅራኄ

ከእነዚህ ሕሙማን መካከል አንዱ ለ፴፰ ዓመታት በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ የነበረ ሰው ነው ። ይህ ሰው ከበሽታው ጽናት የተነሳ ዘመዶቹ ሰልችተውት፣ ጓደኞቹም ርቀውት ብቻውን የቀረ ሰው ነበር። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ወደዚህ ሰው ቀርቦ «ልትድን ትወዳለህን?» ሲል ጠየቀው ።

በሽተኛውም «ጌታ ሆይ፤ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም» በማለት ረዳት ማጣቱን ገለጸ ። ጌታችንም «ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ» አለው ። ያን ጊዜም ድውዩ ወዲያው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ!

ሰንበትን ማክበር

ይህ ታላቅ ተአምር የተፈጸመው በሰንበት ቀን ነበር። አይሁድ በሽተኛው አልጋውን ተሸክሞ ሲሄድ ባዩ ጊዜ «ዛሬ ሰንበት ነው አልጋህን ልትሸከም አይገባህም» በማለት ተቃውሞ አነሡ።

ይሁን እንጂ ጌታችን የሰው ልጅ ከሕግ በላይ መሆኑንና ሰንበት ለሰው እንጂ ሰው ለሰንበት እንዳልተፈጠረ በዚሁ ቀን የታመመወን በመፈወስ በተግባር አስተማራቸው። የመጻጒዕ መፈወስ ሥጋዊ ፈውስ ብቻ ሳይሆን፣ ለዘመናት በኃጢአት አልጋ ላይ ተኝቶ ለነበረው የሰው ልጅ የተሰጠ የነፍስ ድኅነት ምሳሌም ነው ።

የሰንበት መዝሙር

ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ

አምላኩሰ ለአዳም ለዕረፍት ሰንበተ ሠርዐ ወይቤልዎ አይሁድ በዓይ ሥልጣን ትገብር ዘንተ ወይቤሎሙ ኢየሱስ አነኒ እገብር አንትሙኒ እመኑ ለግብርየ ወይቤሎሙ አነ ውእቱ እግዚአ ለሰንበት እግዚኣ ለሰንበት ወልድ ዋሕድ ወይቤሎሙ ብውሕ ሊተ እኅድግ ኃጢአተ በዲበ ምድር እስብክ ግእዛነ ወእክሥት አዕይንተ ዕውራን አቡየ ፈነወኒ

ትርጒም፦
የአዳም ፈጣሪ ለዕረፍት ሰንበትን ሠራ። አይሁድ ይህንን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ ብለው ጠየቁት፤ ኢየሱስም “እኔ እሠራለሁ እናንተም ሥራዬን እመኑ፤ የሰንበት ጌታ እኔ ነኝ” አላቸው። ደግሞም “የሰንበት ጌታዋ ወልድ ዋሕድ ነው!” አላቸው ። [ከዚህ ጨምሮም] “በምድር ላይ ኃጢአትን እተው/ይቅር እል ዘንድ/ ሥልጣን አለኝ፣ ነጻነትንም እሰብክ ዘንድ፣ የዕውራንን ዓይን አበራ ዘንድ አባቴ ላከኝ።” አላቸው።

መንፈሳዊ ትምህርቶች

ከመጻጒዕ ታሪክ የምንማራቸው ዋና ዋና ነጥቦች፦

በአጠቃላይ፣ መጻጒዕ የጌታችንን ኃያልነትና ፈዋሽነት የምናውጅበት፣ የታመሙትን የምናስብበትና እኛም ከነፍስ ደዌያችን እንድንነጻ የምንማጸንበት ቅዱስ ሳምንት ነው ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *