መግቢያ
ዐቢይ ጾም የአጽዋማት ሁሉ የበላይ ወይም “ጉልላት” ተብሎ ይጠራል። ይህ ጾም “እጸድቅ አይል ጻድቅ፣ እነጻ አይል ንጹሐ ባሕርይ” የሆነው አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለማዳን ሰው ከሆነ በኋላ፣ በየጥቂቱ አድጎ የአገልግሎቱ ሁሉ መጀመሪያ፣ የጥምቀቱ ማግስት አድርጎ ለእኛ ለልጆቹ አርአያነትን ያሳየበት ነው። ጌታችን “ከእኔ ተማሩ” (ማቴ. 11:29) እንዳለ፣ ፈለጉን በመከተል ይህንን ታላቅ ጾም እንጾማለን። በዐቢይ ጾም ውስጥ ስምንት (8) ዓበይት ሳምንታት ያሉ ሲሆን፣ እነዚህም፦ ዘወረደ፣ ቅድስት፣ ምኩራብ፣ መጻጉዕ፣ ደብረ ዘይት፣ ገብር ኄር፣ ኒቆዲሞስ እና ሆሳዕና በመባል ይታወቃሉ። አሁን ከእነዚህ ሳምንታት መካከል የመጀመሪያው ላይ እንገኛለን።
የሳምንቱ ስያሜና ትርጉም
ዘወረደ ማለት “ከላይ የመጣ፣ የወረደ” ማለት ነው። ይህም የአምላካችንን ሰው መሆን (ምሥጢረ ሥጋዌን) ያመለክታል። ጌታችን ለኒቆዲሞስ ስለ ሰማያዊ ምሥጢር በነገረው ጊዜ “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” (ዮሐ. 3:13) በማለት የተናገረውን መሠረት በማድረግ ሳምንቱ በዚህ ስያሜ ይጠራል።
ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በዚሁ ሳምንት ዕለተ ሰንበት በሚዘመረው ቃለ እግዚአብሔር፦ “አዳምን ለማዳን ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፤ የሰማይን ሥልጣን ያለው የሁሉ ጌታ እንደሆነም ምንም አላወቁም” ብሎ ተቀኝቷል። አምላክ አዳምና ዘሩን ሊያድን ከሰማይ ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም በመወለዱ፣ እኛም በጾሙ መጀመሪያ “ወረደ፣ ተወለደ” የሚለውን የማዳን ሥራውን መሠረት በማሰብ እንጀምራለን።
ሌሎች መጠሪያዎች እና ታሪካዊ አመጣጣቸው
ይህ የመጀመሪያው ሳምንት በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሌሎች ሦስት መጠሪያዎች አሉት፦
- ጾመ ሕርቃል፦ ይህ ስያሜ የተገኘው በ614ዓ.ም ከነበረው የቤዛንታይን ንጉሥ ሕርቃል ታሪክ ነው። በዘመኑ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር። ንጉሡ መስቀሉን ለማስመለስ ሲነሳ፣ ትልቅ ክርስቲያን ነበርና አንድ ሃሳብ ይፈትነዋል። ጭንቀቱንም ለኢየሩሳሌም ሕዝብ “ሐዋርያት ሰውን የገደለ እድሜውን በሙሉ ይጹም ስላሉ እንዴት ይህንን ሕግ እንዴት ላድርገው” ብሎ ያስረዳቸዋል። በኢየሩሳሌም የነበሩ ምእመናንም “አንተ መስቀሉን አስመልስልን እንጂ እኛ የአንድ ሰው እድሜ ሰባ ሰማንያ ዓመት ነውና ጾሙን አምስት አምስት ቀን ተከፋፍለን እንጾምልሃለን” ብለውታል። ስለዚህ ይህ ጾም በዚህ ቃልኪዳን መሠረት፣ የኢየሩሳሌምን ምእመናን ፈለግ በመከተል ለወንድም፣ እኅቶቻችን፤ መስቀሉን ወደእኛ ለማቅረብና በዘመናችን በጦርነት የሚዋጉን ልዩ ልዩ የሥጋ ፍላጎቶቻችን ድል ለማድረግ በትሕትና የተገለጸ አምላክን ገንዘብ በማድረግ የምንጾመው ጾም ነው። “ጾመ ሕርቃል” ያሰኘውም ይኸው ነው።
- ሙሴኒ (ዘመነ ሙሴ)፦ እግዚአብሔር አምላክ ለነቢዩ ሙሴ “ሕዝብህ፣ የከብትህ መንጋህና ቤተሰብህ ሁሉ በሰንበት ቀን ከድካማቸው ይረፉ” ብሎ ማዘዙንና የሰንበትን ክብር መግለጡን በማሰብ ይጠራል።
- ዘመነ አዳም፦ አምላክ አዳምን ፍለጋ ከሰማይ መውረዱንና ለአዳም የገባውን የድኅነት ቃል ኪዳን መፈጸሙን ስለሚያዘክር በመጀመሪያው ሰው በአዳም ስም ይጠራል።
በዚህ ሳምንት የሚከወኑ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሥርዓቶች
በዘወረደ ሳምንት የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ለየት ያለ ይዘት ይኖረዋል፦
- ያሬዳዊዜማ (ጾመድጓእናምዕራፍ)፦ በዚህ ሳምንት የሚዘመሩት ዜማዎች በሙሉ የጾምን፣ የጸሎትን፣ የምጽዋትንና የፍቅርን ጠቃሚነት አጉልተው የሚያስተምሩ ናቸው። በተለይም “ምዕራፍ” የተባለው የዜማ መጽሐፍ በጾመ ዐርባ ብቻ ለአገልግሎት የሚውል ክፍል አለው። ይህንን ዜማ ለመማር 150 መዝሙረ ዳዊትን፣ 15 የነቢያት ጸሎቶችንና 5 መኃልየ መኃልያተ ሰሎሞንን በቃል ማጥናት ይጠበቃል። ለእያንዳንዱ ሳምንትም ራሱን የቻለ ቃለ እግዚአብሔር ይገኝበታል። በዚህ በዘወረደ ሳምንትም ሊቃውንቱ (መዘምራኑ) ከሌሊት ይዘው እኒህን ምስጋናዎች ደከመን ሳይሉ በዐቢይ ዜማ በኅብረት ያሰማሉ።
- አርምሞ (ዝምታ)፦ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ መነኮሳትና በርትተው የሚጾሙ ምእመናን የአርምሞን (የዝምታን) ጸጋ ገንዘብ ያደርጋሉ። በቤተ ክርስቲያንም ጸናጽልና ከበሮ ታስቀምጣለች። ከንዋያተ ቅድሳቱ ድምጽ ይልቅ “በጾም የተጎሰመ ሥጋ የሚጮኸው ጩኸት፣ የሚያቀርበው ምሥጋና” ይበረታልና።
ጾም፦ትእዛዝወይስፈቃድ?
ጾምን መጾም የፈቃድ ብቻ ሳይሆን የትእዛዝም መሆኑን መገንዘብ ይገባል። በብሉይ ኪዳን ነቢዩ ኢዩኤል “ጾምን ቀድሱ፣ ምሕላንም ዐውጁ” (ኢዩ. 1:11) እንዳለ፤ በአዲስ ኪዳንም ቅዱስ ጳውሎስ “በጾም፣ በንጽሕና ተወስናችሁ እግዚአብሔርን አገልግሉ” (2ቆሮ. 6:4-6) ብሏል። ጌታችንም ራሱ በሞት ከተለያቸው በኋላ ሐዋርያት እንደሚጾሙ ተናግሯል (ማቴ. 9:15)። ስለሆነም ጾም የሥጋን ፈቃድ ለነፍስ ማስገዣ ታላቅ መሣሪያ ነው።
ምክረ አበውና መንፈሳዊ ዝግጅት
በዚህ በተቀደሰ ሳምንት አባቶቻችን የሚከተሉትን ነጥቦች እንድንገነዘብ ይመክሩናል፦
- እግዚአብሔርን እንዳይቆጣ ስንፍናን አስወግደን በትጋት ተግባረ ነፍስን መያዝ።
- ያየነውንና የሰማነውን እውነት መመስከር።
- ትሕትናን መለማመድ፤ አምላክ ከሰማይ የወረደው በትሕትና ነውና እኛም በጾማችን ወቅት ራሳችንን ዝቅ ማድረግን ገንዘብ እንድናደርግ መትጋት።
በሳምንቱ መግቢያ የሚባለው የቅዳሴ ምስባክ (መዝሙር 2:11)፦ “ተቀነዩለእግዚአብሔርበፍርሀት፣ወተሐሰዩሎቱበርዓድ፤አፅንዕዋለጥበብከመኢይትመአዕእግዚአብሔር።” (ትርጉም፦ ለእግዚአብሔር በፍርሀት ተገዙ፣ እርሱንም በማምለክ ደስ ይበላችሁ፤ እግዚአብሔር እንዳይቆጣ ጥበብን አፅንታችሁ ያዙ።)
ምክረ አበውና መንፈሳዊ ዝግጅት
ዘወረደ አምላክ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር የገለጸበት፣ ከልዕልናው ወርዶ ትሕትናን ያስተማረበት ሳምንት ነው። እኛም ይህን ጾም ስንጾም እንደ ጌታችን ትሑታን በመሆን፣ የሥጋ ፍላጎታችንን ለነፍሳችን በማስገዛትና ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ሊሆን ይገባናል።
ይቆየን!