Divine Liturgy Service Hours: Saturday @ 5:00 am – 8:00 am | Sunday @ 4:00 am – 7:00 am

፩. መግቢያ፡ ከዝግጅት ወደ ተጋድሎ

የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት (ዘወረደ) የጾሙ መግቢያና የአምላክ ሰው የመሆን ምስጢር የሚነገርበት ዝግጅት ነው። የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት “ቅድስት” በመባል ይታወቃል ። ሳምንቱ ስያሜውን ያገኘው የቤተ ክርስቲያን የዜማ መጋቢ በሆነው በሊቁ በቅዱስ ያሬድ አማካኝነት ነው ።  ቅድስት ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአርባ ጾም ድል የነሳበትን፣ ሰው ለሥጋው ሳይሳሳ ለነፍሱ እያደላ እንዲጾም አርአያነቱን ሊያስተምረን የጀመረበት የመጀመሪያው ሳምንት ነው። ጌታችን በገዳመ ቆሮንቶስ መጾም የጀመረበትን የምናስበው በዚህ ሳምንት ነው፤ እኛም የእሱን ፈለግ ተከትለን ወደ መንፈሳዊ ተጋድሎ የምንገባበት ወቅት ነው።

፪. የሳምንቱ ስያሜና ትርጓሜ

የቤተ ክርስቲያናችንን መዝሙር ንባቡን ከዜማው አስማምቶ ያቀረበልን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፣ በጾመ ድጓው ለዐቢይ ጾም እሑዶች ሁሉ የተለየ መዝሙር ሠርቶላቸዋል። በዚህም መሠረት ሁለተኛው እሑድ ቅድስት ይባላል።

፫. ሦስቱ የቅድስት ሳምንት ዓበይት ነጥቦች

በዚህ ሳምንት በቤተ ክርስቲያናችን በሚሰጠው ትምህርት ሦስት ዋና ዋና ነጥቦች ጎልተው ይወጣሉ፦

  1. እግዚአብሔር በባሕርይው ቅዱስ ነው፦ ቅዱስ ማለት ልዩ፣ ክቡር ማለት ሲሆን የእርሱ ቅድስና ከማንም ያላገኘው የባሕርይ ገንዘቡ ነው። እኛም ዕለት ዕለት “ይትቀደስ ስምከ፤ ስምህ ይቀደስ” የምንለው ለዚህ ነው።
  2. ክርስቶስ በደሙ ቀደሰን፦ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ በከበረ ደሙ ዋጀን፤ ከበደላችንም አነጻን (፩ ዮሐ ፩፥፯)። በውድ ልጁም በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን።
  3. በቅድስና ሕይወት እንድንኖር ተጠርተናል፦ “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” (፩ ጴጥ ፩፥፲፭) ተብሎ በተጻፈው መሠረት፣ በኑሮአችን ሁሉ ቅዱሳን የመሆን መንፈሳዊ ግዴታ አለብን።

፬. የሰንበት ቅድስናና ሥርዓተ ቤተክርስቲያን

ቅዱስ ያሬድ በዚህ ዕለት እንደሚዘምረው፣ ሰንበት ነገረ እግዚአብሔር በተለየ ሁኔታ የሚዘከርባት ቅድስት ዕለት ናት።

፭. የዕለቱ ምስባክና ወንጌል

ምስባክ (መዝሙር፺፭፥፭-፮)፦ “እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ፈጠረ። ምስጋናና ክብር በፊቱ ናቸው፤ ቅድስናና የግርማ ታላቅነት በመቅደሱ ውስጥ ናቸው።”

ወንጌል (ማቴዎስ፮፥፲፮-፳፭)፦ ጌታችን ስለ እውነተኛ ጾም ያስተማረበት ክፍል ይነበባል። “ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ… አንተ ግን ስትጾም በስውር ላለው አባትህ እንዲታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ” በማለት የልብ ቅድስናን ያሳስበናል።

፮. ቅድስናን ገንዘብ የማድረጊያ መንገዶች

አምላካችን “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” (ዘሌ. ፲፱፥፪) በማለት በቅድስና ሕይወት እንድንመላለስ አዝዞናል ። ይህንን የተሰጠንን የጸጋ ቅድስና ጠብቀን ለመኖርና ገንዘብ ለማድረግ ከአምላክ ቸርነት ቀጥሎ በሚከተሉት መንፈሳዊ ተግባራት መትጋት ይገባናል፦

. የክርስቶስቤዛነትለቅድስናችን

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው ቤዛ ሆኖ በከበረ ደሙ ሊቀድሰን ነው (አርዓያነቱ ሳይዘነጋ)። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው፣ እንደ ጸጋው ባለጠግነት መጠን በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንንና የኃጢአት ስርየትን አግኝተናል ። የእርሱ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። ከኃጢአት መለየት ደግሞ የቅድስና መጀመሪያም፣ ፍጻሜም ነው።

ቅድስና የተፈቀደልን ብቻ ሳይሆን የታዘዝነውም ጭምር ነው። ወደ ቅድስና የሚመሩን መንገዶች፦

ማጠቃለያ

“ቅድስት” በሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል ለቅድስና ሕይወት ምልክትና ማስታወሻ ናት። ስለዚህ በዚህ በተቀደሰው ሳምንት፣ በትጋት ጾመንና ጸልየን፣ ከኃጢአት ርቀንና በንስሐ ታድሰን የቅድስናን ሕይወት ገንዘብ ልናደርግ ይገባል። አምላካችን እግዚአብሔር በዚህ ሳምንት በረከቱን ያድለን፤ በቸርነቱ ተቀድሰን ለትንሣኤው ብርሃን እንዲያበቃን የዘወትር ጸሎታችን ይሁን።

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃና የቅዱሳን በረከት አይለየን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ይቆየን!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *