Divine Liturgy Service Hours: Saturday @ 5:00 am – 8:00 am | Sunday @ 4:00 am – 7:00 am

የብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ መልክእት

እግዚአብሔርን የምታመልኩ፣ የምትወዱ፣ የምታገለግሉ የመንፈስ ልጆቼ ከሁሉ አስቀድሜ እንኳን ለዛሬዋ ቀን በሰላምና በፍቅር አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ። እግዚአብሔር አምላክ ስደተኞችን በስደት ዓለም የሚገዳደሩ ፈተናዎች ሲገጥማቸው መለኮታዊ ጥበቃውን በማድረግ ሊመጣ ካለው እና ከመጣው ሁሉ ይጠብቃቸዋል። መዝሙረኛው ዳዊት “ እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃቸዋል” ሲል የዘመረው አበውን እና እመውን በስደት ሀገር የጠበቃቸው እግዚአብሔር ስለሆነ ነው። ውድ የሆናችሁ የመንፈስ ልጆቼ ዛሬም የእግዚአብሔር ጥበቃ ከእኛ ጋር ስለሆነ ደስ ይበላችሁ። የተወደዳችሁ ልጆቼ ጥበቃ የሌለው ስደት ከእግዚአብሔር ፊት መሰደድ ነውና ከእግዚአብሔር ፊት አትጥፉ። በጸሎት እየተጋችሁ፣ በንስሐ እየታጠባችሁ፣ በቅዱስ ቁርባን እየታተማችሁ ወደ ፊት ትመሙ። ሁሉን በቸርነት የሚጠብቅ እግዚአብሔር በስደት ስንኖር ከሚመጣብን መከራ ሥጋ መከራ ነፍስ ይጠብቀን። የዱባይ ደብረ መዊእ ቀሳውስት፣ዲያቆናት፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የክብረ ቅዱሳን ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት፣ ወላጆችና ባለትዳሮች፣ የጽዋዕ ማኅበራት፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ልጆች እንዲሁም ምእመናን እግዚአብሔር ይባርካችሁ፣ይቀድሳችሁ።