እንኳን ደና ወደ ቤተ ክብረ ቅዱሳን መጡ
የዱባይ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ወቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን የክብረ ቅዱሳን ሰንበት ትምህርት ቤት እንደሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የሰንበት ትምህርት ቤቶች እግዚአብሔርን የሚያመልክና ክብር ለሚገባቸው የእግዚአብሔር ቅዱሳን ክብርን የሚሰጥ፣ በፈቃዱ ራሱን ለአገልግሎት የሚለይ፣ በሚያልፍ ዓለም እየኖረ የማታልፈውን መንግሥተ ሰማያት ተስፋ የሚያደርግና በእግዚአብሔር ቸርነት እየታገዘና በቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ እየተማመነ መንፈሳዊ ሕይወቱን የሚያንፅ በአጥቢያችን የሚገኙ ምእመናንን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር በመሰብሰብ ትምህርተ ሃይማኖትን እንዲማሩ፣ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት፣ ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት በማወቅ እንዲተገብሩና በፈሪሃ እግዚአብሔር እየኖሩ ፈጣሪያቸውን ዘወትር የሚያመሰግኑ፤ ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን የሚቀበሉ በእድሜ የማይወሰን ትውልድን ማፍራት ዋና ዓላማው ነው።
ቤተ ክብረ ቅዱሳን የተመሰረተው በ2011ዓ.ም ሲሆን በአሁኑ ግዜ ወደ 200 የሚደርሱ አባላትን በማሳተፍ በአባላቱ ታዛዥነት፤ በየ፫ ዓመቱ በሚመረጡ አመራሮች ትጋት እንዲሁም በአባታችን ቀሲስ ደረጀ ጂማ ያላሰለሰ እገዛ እና ድጋፍ ሰንበት ትምህርት ቤታችን አሁን ካለበት ደረጃ ላይ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሊደርስ ችሏል።
ሰንበት ትምህርት ቤታችን ዘወትር ቅዳሜ እና እሑድ ከቅዳሴ አገልግሎት በኋላ እንዲሁም ዕሮብ በሚኖረው አገልግሎት ላይ ያሬዳዊ ዜማን የጠበቁ መዝሙሮች፣ በየዓመቱ በሚከበሩ የቤተ ክርስቲያናችን በዓላት እና ጉባኤያት እንዲሁም በጌታችን ዐበይት በዓላት ላይ መዝሙርን እና ኪነጥበብን እንዲሁም ትምህርታዊ ጥያቄ እና መልስ ፤ጭውውቶችንና መንፈሳዊ ድራማዎችን በማቅረብ አባላቱን ከማስተማር ባሻገር አገልግሎቱን ለምእመናንም ጭምር እንዲዳረስ በማድረግ ላይ ይገኛል ።


