እንኳን ደና ወደ ቤተ ካህናት መጡ
በዱባይ ደብረ መዊእ ቅዱስ ሚካኤል ወቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን የሚገኘው ይህ የካህናት ማኅበር በውስጡ ደብሩን በቀናነት የሚያገልገሉ ቀሳውስት አባቶችን፣ መምህራንና ዲያቆናትን የያዘ ነው። በአሁኑ ሰዓት 9 ቀሳውስት እና ከ30 በላይ ዲያቆናትን ይዞ ማገልገል ችሏል። ካህናቱ ምሥጢራትን በመፈጸም፣ በትምህርት፣ በምክር፣ በአበ ነፍስነትና በዝማሬ እያገለገሉ ይገኛሉ። ማህበሩ ደብሩን ከሚያገለግልባቸው ዘርፎች መካከል ዋነኞቹ፡
ቅዳሴ
በደብራችን በዓመቱ ውስጥ ባሉት ሁሉም ቅዳሜንና እሁዶች፣ ወርኃዊ የቅዱስ ሚካኤልና የቅድስት ሥላሴ በዓላት እንዲሁም በዐቢያን ዕለታት ቅዳሴ ይቀደሳል።
ትምህርተ ወንጌል
ካህናቱና ዲያቆናቱ የቀናች ሃይማኖታችንን በመከተል ለእያንዳንዱ የደብሩ ክፍላት አባላት በተለያየ መንገድ በበይነ መረብ፣ ቅዳሜ በሚካሄዱ የማህበር ጉባኤያት ላይ በአካል ትምህርቶች (ለወላጆች፣ ለከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች፣ ለክብረ ቅዱሳን ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና ልጆች) ይሰጣሉ።
የደብሩን ምዕመናን የንስሓ ሕይወት በተመለከተ
በደብሩ ውስጥ ወደ 50 የሚጠጉ የጽዋዕ ማኅበራትና ሰባት የአገልግሎት አምዶች የሚገኙ ሲሆን እነዚህም ደግሞ በየራሳቸው ምዕመናንን አቅፈው ይዘዋል። ለእነዚህ ሁሉ የሚሆን የንስሓ አባት፣ የነፍስ ተጠሪ በዚህ በደብራችን በሚገኙ ካህናት በኩል መሆን ስላለበት የደብሩ ካህናት ምዕመናንን በንሰሃ አባትነት እየመከሩ እና እየገሰጹ በሃይማኖት በመጠበቅ ያገለግላሉ።


