፩. መግቢያ፡ስያሜና ምንነት
ምኩራብ ማለት በቀጥታ ትርጉሙ “መሰብሰቢያ” ወይም “መማሪያ” ማለት ነው። ቅዱስ ያሬድ የጌታን ጾም ሳምንታት በሰየመበት ስያሜው ሦስተኛውን ሳምንት ጌታ በምኩራብ ማስተማሩን፤ መስበኩንና መፈወሱን ለማስታወስ ምኩራብ ብሎ ሰይሞታል። የምኩራብ ሥርዓት የተጀመረው በባቢሎን ነው። እስራኤላውያን በናቡከደነጾር ተማርከው ወደ ባቢሎን ሲሄዱ፣ የነበረው አንድ መቅደስ (የሰሎሞን መቅደስ) ፈርሶ ነበር። በኦሪት ሕግ መሠረት ደግሞ በባዕድ ሀገር መቅደስ መሥራት አይፈቀድም ነበር (መሥዋዕት የሚሰዋው በኢየሩሳሌም ብቻ ስለነበር)።
- መፍትሔው፦ አይሁድ አምላካቸውን እንዳይረሱ፣ ሕጉን (ኦሪትን) እንዲያጠኑና እንዲጸልዩ በየሰፈራቸው ትናንሽ የመሰብሰቢያ ቦታዎችን ሠሩ። እኒህ መሰባሰቢያዎችም “ምኩራብ” ተባሉ።
- ከመቅደስ በምን ይለያል?፦ በመቅደስ ውስጥ መሥዋዕት ይቀርባል፤ በምኩራብ ውስጥ ግን ትምህርት፣ ጸሎትና ንባብ ብቻ ይከናወናል።
ይህም አገልግሎት እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላም የቀጠለ ሲሆን በተለያዩ ሥፍራዎች ተስፋፍቶ በየሰንበቱም ብዙ ሕዝብ ወደ ምኩራቦች ይሰበሰብ ነበር። (ሐዋ 9፥2 ፤ 13፥3)
፪. የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምኩራብ አገልግሎት
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ ወደእነዚህ ምኩራቦች በተደጋጋሚ በመገኘት አስተምሯል፤ የመንግስትንም ወንጌል ሰብኳል፤ በሕዝብም ዘንድ እየተመላለሰ የሥጋ ደዌንና ሕማምን በተዓምራት ፈውሷል፡፡ (ማቴ.4÷23፤ ማር.1÷39)፡፡ በአንድ ምኩራብ የሚሰባሰቡት ሰዎች ጥቂት ሰዎች ስለሆኑ ለማስተማር ቀላልና የእያንዳንዱን አማኝ ሐሳብና ራዕይ ለማወቅም የሚያስችል ነው። ጌታ በአንድ ምኩራብ በተደጋጋሚና ባለመሰልቸት ከመቅደስ ይልቅ እየተገኘ ማስተማሩን ወንጌል እንዲህ ይመሰክርልናል ”እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፥ ሊያነብም ተነሣ።”(ሉቃ.4÷16)
አምላካችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደእነዚህ ምኩራቦች እየገባ ያስተማረበትንም ምክንያት እንደሚከተለው መመልከት ይቻላል፦
- ሥርዓት አክባሪነትን ለማስተማር፦ ጌታችን ሰንበትን የሚያከብረው በምኩራብ ተገኝቶ በማስተማር ነበር። ይህ የሚያሳየው ሕግን የሠራ እርሱ የኦሪትንም ሕግና ሥርዓት እንድሚያከብርና ትምህርቱም በተግባር የሚገለጽ መሆኑን ነው።
- ተደራሽነት፦ በመቅደስ ውስጥ በዓመት ጥቂት ጊዜ ለሚመጣው ትልቅ ሕዝብ ከመስበክ ይልቅ፣ በምኩራብ በየሳምንቱ ከሚገናኙት ጥቂት አባወራዎች ጋር መቆየትን መርጧል። ይህ “የቅርብ አገልግሎት” ይባላል።
- ፈውስና ትምህርት፦ ጌታ በምኩራብ ውስጥ በቃሉ ብቻ ሳይሆን በተዓምራትም (በመፈወስ) የመንግሥተ ሰማያትን ወንጌል ሰብኳል።
ሐዋርያትም እንደጌታ ልማድ እንዲሁ በመቅደስ እየተገኙ በተደጋጋሚ አስተምረዋል፡፡ “በስልማናምበነበሩጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ”(ሐዋ.13÷5)፡፡“ በአንፊጶልና በአጶሎንያም ካለፉ በኋላ ወደ ተሰሎንቄ መጡ፥በዚያም የአይሁድ ምኵራብ ነበረ። ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ እነርሱ ገባ፥ሦስት ሰንበትም ያህል ከእነርሱ ጋር ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ይነጋገር ነበር…”(ሐዋ.17÷1-2)፡፡
ይህ ሳምንት ለዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው ትልቅ ትምህርት “አገልግሎት” በመቅደስ ቅጥር ብቻ መወሰን እንደሌለበት ነው። የምኩራብ አገልግሎት ለአማኙ የግል ሕይወትና ችግር ቅርብ የሆነ የአገልግሎት ዓይነት ነው። ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ወደ መቅደሱ እስኪመጡ ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ፣ ልክ እንደ ጌታችንና እንደ ሐዋርያት ሁሉ ወደ ሕዝቡ መንደርና ቤት በመውረድ የሰዎችን ችግር የሚረዳና የሚያጽናና አገልግሎት መስጠት ይገባታል። ይህም አማኙን ከውጫዊ ሥርዓት ባለፈ በቃለ እግዚአብሔር ታንጾ ለሥጋ ወደሙ እንዲበቃና እውነተኛ ክርስቲያናዊ ሕይወት እንዲመራ ይረዳዋል።
- የዕለቱ ምንባባትና መዝሙር ምስጢር
- የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ ቦአ ምኩራቦሙ ወገሠፆሙ ያርምሙ አንከሩ ምህሮቶ ሞገስ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕሣዓ አፉሁ፡፡
ትርጉም:- ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም የሰንበት ጌታዋ ነው ፡፡ያባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል (እያለ የሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው፡)፡ ወደ ምኩራባቸውም ገብቶ ዝም ይሉ ዘንድ ገሠፃቸው፤ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ።
፫. ምንባባት
ቤተ ክርስቲያን በዚህ ሳምንት የምታነባቸው ክፍሎች ሁሉም አንድ መልእክት አላቸው፦
- ምስባክ (መዝ.68፡9፡-) እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ፤ ትዕይርቶሙ ለእለይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ፤ ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡
- ትርጉም፦ የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና ነፍሴን በጾም አስመረርኋት፡
- ወንጌል (ዮሐ. 2÷12-ፍጻ.)፦ ጌታ ቤተ መቅደሱን ከንግድ ቦታነት ሲያጸዳው እናያለን። ይህ የሚያሳየው ልባችንና ቤተ መቅደሳችን ለእግዚአብሔር ጸሎት እንጂ ለምድራዊ ጥቅም መዋል እንደሌለበት ነው። ከዚያ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን ሰላማዊው ኢየሱስ ክርስቶስ በማይናወጽ ዓለት ላይ የመሠረታት በከበረ ደሙ ያተማት ናት። የክርስቶስን መዓዛ የምናሸትባት ክርስቶስን ራሱን የምናይባት ቅድስት ልዩ የሆነች መንግሥት ናት። የሰው ልጅ በዓለም ሳለ ለዓይኑ መልካምን ነገር ማየት ለጆሮው መልካምን ነገር መስማት ጊዜያዊ ቢሆንም ሰላም እንዲሰማው ያደርገዋል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን እውነተኛውን ምንጩ የማይነጥፈውን ዘለዓለማዊውን ሰላም ትሰጣለች። በዓለም ምናምንቴ ምክንያት ያጣናውን ሰላም ዕለት ዕለት ትለግሠናለች። የእውነተኛ ዕረፍት ምንጭ ናት። ዓለምን የሚማርክ ኃያል የሆነ ውበት አላት። ሰሎሞን በመኃልየ መኃልይ “ይህች እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጎበኝ እንደ ጨረቃ የተዋበች እንደ ፀሐይም የጠራች ዓላማ ይዛ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ማን ናት” ይላታል። (መኃ.፮፥፲) ጨረቃ ብርሃኗን ከፀሐይ የምታገኝ ቢሆንም ግርማና ውበት ተሰጧታልና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጨረቃ ተመሰለች። (ኢዮ.፴፩፥፳፮) ክርስቶስ ይህን ውበት የሚያደበዝዙትን እጅግ ይቃወማል። ለዚያም ነው ቤተ መቅደሱን ገበያ አድርገውት ባገኛቸው ጊዜ ከወትሮ የተለየ የተቆጣው። ገበያ አንድ ቀን ማትረፍ አንድ ቀን መክሰር አለበት። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን ዘወትር ማትረፍ ነው። ብንኖርም ብንሞትም ትርፍ ነው። ገበያ አንድ ቀን ርካታ አንድ ቀን ርኃብ ያለበት ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን ለዘለዓለም የማያስርብ ለዘለዓለም የማያስጠማ መብል መጠጥ ያለባት ናት። ገበያ ሽንገላ አለበት፤ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን ሁል ጊዜ ጽድቅ አለ። ገበያ ሥስት፤ ራስ ወዳድነት፣ ፍቅረ ንዋይ አለበት። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን ፍጹም የሆነ ሕግ ፍቅር፣ ጠላትን መውድድ ያለባት ናት። በሰዓቱ ክርስቶስ “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ” ብሎ የገሠፃቸውና ወደ ምኩራብ በገባ ጊዜ በዚያው ስፍራ ያገኛቸውን አይሁድን ለቤተ መቅደሱ ተቆርቋሪ የሚመስሉትን ከእነርሱ በላይ ለእግዚአብሔር ቅርብ እንደሌለ አድርገው የሚያስቡትን ነበር።
- ቅዱስ ጳውሎስ (ቆላ. 2÷16-ፍጻ.)፦ በውጫዊ ሥርዓትና “አትዳስስ፣ አትንካ” በሚል ሕግ ብቻ መታጠር ሳይሆን፣ ከራስ ጋር መጣበቅና በመንፈስ ማደግ እንደሚገባ ይገልጻል።
- ቅዱስ ያዕቆብ (ያዕ. 2÷14-ፍጻ.)፦ “እምነት ያለ ሥራ የሞተ ነው” ይላል። ዝም ብሎ መቅደስ መሄድ ብቻ ሳይሆን ለታረዘውና ለተራበው መድረስ (ምኩራብነት) ትክክለኛ እምነት መሆኑን ያስረዳል።
፬. ማጠቃለያ
ምኩራብ የዓቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት ሲሆን፣ ጌታችን በምኩራብ ገብቶ ያስተማረውንና የፈወሰውን ተግባር ለማሰብ በቅዱስ ያሬድ የተሰየመ ነው። ምኩራብ የተጀመረው አይሁድ በባቢሎን ምርኮ ሳሉ የኢየሩሳሌም መቅደስ በመፍረሱ ምክንያት፣ በየሰፈራቸው ተሰብስበው ለመማርና ለመጸለይ በሠሩት አነስተኛ ቦታ ነው። ጌታችንም ወደ ሕዝቡ ለመቅረብና የእያንዳንዱን ችግር ለመረዳት ሲል በየምኩራቡ ገብቶ ማስተማርን ልማድ አድርጎት ነበር። ይህ ሳምንት ለዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው ትልቅ መልእክት፣ አገልግሎት በመቅደስ ብቻ መወሰን እንደሌለበትና አገልጋዮች አማኙ ባለበት አድራሻ ሄደው ማስተማርና መርዳት እንዳለባቸው ነው። በዕለቱ የሚነበቡት የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎችም እምነት ያለ መልካም ሥራ ትርጉም እንደሌለውና የእግዚአብሔር ቤት ለንግድ ሳይሆን ለጸሎትና ለምሕረት ብቻ መዋል እንዳለበት ያስገነዝቡናል።ባጭሩ “ምኩራብ” ማለት፦
- እግዚአብሔርን በየቦታውና በየሰፈሩ መፈለግ፣
- ቃሉን በጥልቀት ማጥናትና መረዳት፣
- አገልጋይ ወደ ሕዝቡ ቤትና ሕይወት ዝቅ ብሎ መውረድ፣
- እምነትን በምሕረትና በቸርነት ሥራ መግለጥ ማለት ነው።
በዚህ በተቀደሰው ሳምንት፣ በትጋት ጾመንና ጸልየን፣ ከኃጢአት ርቀንና በንስሐ ታድሰን የቅድስናን ሕይወት ገንዘብ ልናደርግ ይገባል። አምላካችን እግዚአብሔር በዚህ ሳምንት በረከቱን ያድለን፤ በቸርነቱ ተቀድሰን ለትንሣኤው ብርሃን እንዲያበቃን የዘወትር ጸሎታችን ይሁን።
የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃና የቅዱሳን በረከት አይለየን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ይቆየን!
ምንጭ፡ https://eotcmk.org/a/ምኩራብ-2/