Divine Liturgy Service Hours: Saturday @ 5:00 am – 8:00 am | Sunday @ 4:00 am – 7:00 am

ሦስቱ የእምነት መሠረቶች / አዕማድ /

ዶግማ (Dogma)

ቃሉ የግሪክ (የፅርዕ) ነው። ትርጉሙም የማይለወጥ፥ የማይሻሻል፥ የማይቀየር ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉ “ዶኪን” ከሚለው የግሪክ አንቀጽ የተገኘ ነው፡፡ በጥንቱ ግሪክኛ ቋንቋ “ዶኪን ሚ” የሚለው አገላለጽ ወደ አማርኛ አገላለጽ ሲቀየር “ወስኜዋለሁ፣ እርግጠኛ ነኝ፣ ጽኑ እምነቴ ነው” ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዶግማ ማለት እርግጠኛ የኾነ ነገር፣ የተወሰነ ነገር፣ የታመነ ነገር ነው፡፡

ቀኖና (Canon)

የጽርዕ (የግሪክ) ቃል ሲኾን ትርጉሙም ሕግ፥ ሥርዓት፥ ደንብ፥ የቅጣት መጠንና ልክ፥ መለኪያ ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉ “ካኖን” ከሚለው ቃል የተገኘ ነው፡፡ ቀኖና የሚለው ቃል በሥነ ጥበብ፣ በሕግ፣ በፖለቲካ እና በቤተ ክርስቲያን እየገባ አገልግሎት ላይ ይውላል፡፡ በተጨማሪም ምዕመናን ከንስሐ አባታቸው የሚቀበሉት ወይም የሚታዘዙት ጾም፥ ጸሎት፥ ስግደትና ምጽዋት ቀኖና ይባላል፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ተነሳሂውን ወደ ትክክለኛው የሕይወት መንገድ ለማምጣት የሚሰጡ ስለኾነ ነው፡፡

በዋናነት ቀኖናን “ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን” በሚለው መረዳት ይቻላል (2ተሰ. 3፥6፣ 2ተሰ. 3፥14፣ 1ቆሮ. 14፥40፣ 1ቆሮ. 11፥46)።

ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ከየት መጣ?
ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በደብተራ ኦሪት፣ ደብተራ ድንኳንና በመቅደሰ ኦሪት የነበሩ የአምልኮ እና የአሠራር ሥርዓቶች ለዛሬው ቀኖና ወይም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በመነሻነትና በምንጭነት ያገለግላሉ፡፡

  • “ያለ ሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ኹሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን፡፡” 2ተሰ. 3፥6
  • “ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገስጿቸው” 2ተሰ. 5፥14
  • “ኹሉ በአግባብና በሥርዓት ይኹን” 1ቆሮ. 14፥40

የቀኖና ምንጮች ዋና ዋናዎቹ፡-

  1. የሐዋርያት ሲኖዶስ፡- (ሥርዓተ ጽዮን፣ አብጥሊስ፣ ትዕዛዝ እና ግጽው የተባሉ 4 ክፍሎች አሉት)። እንዲሁም ዲድስቅሊያ (የተባለ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን ያስተምራል)።
  2. ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ጉባኤያት፡-
    • ጉባኤ ኒቂያ (በ325 ዓ.ም – 20 ቀኖናዎች ተደንግገዋል)
    • ጉባኤ ቁስጥንጥንያ (በ381 ዓ.ም – 7 ቀኖናዎች)
    • ጉባኤ ኤፌሶን (በ431 ዓ.ም – 8 ቀኖናዎች ተደንግገዋል)
  3. መጽሐፍ ቅዱስ፡- (1ቆሮ. 11፥25፣ 1ቆሮ. 4፥7፣ ሉቃ. 1፥1–4)
  4. ብሔራውያን ጉባኤያት፡- በየሀገራቸው ሲኖዶስ ጉባኤያት የተደነገጉት ከእነዚህ ጋር በተጠቃሽነት ይነሣሉ፡፡ (ለምሳሌ፡- የዕንቆራ ጉባኤ፥ የቅርጣግና ጉባኤ፣ የጋንግራ ጉባኤ፣ የአንጾኪያ ጉባኤ፣ የሎዶቅያ ጉባኤ እና የሰርዲቅያ ጉባኤ ተጠቃሽ ናቸው)።
  5. የአበው ውሳኔ፡- ከዓለም አቀፍም ኾነ ከብሔራውያን ጉባኤያት በተጨማሪ በአበው ልዩ ልዩ ቀኖናት ተወስነዋል፡፡ ከእነዚህ ቀኖናት መካከል፡-
    • የሮማው ሊቀ ጳጳስ አቡሊዲስ ፡- የደነገጋቸው ቀኖናት በምኅጻረ – ቃል (በደስ) ይባላል፡፡
    • ባስልዮስ ፡- ክህነትን፥ ብቻንና ምንኩስናን በተመለከተ (ባስ)።
    • ኤጲፋንዮስ ፡- የካህናትን፥ የምዕመናንን ሥነ – ምግባር በተመለከተ።
    • ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ ፡- የሠራቸው ቀኖናት (ግር)።
    • ዮሐንስ አፈወርቅ ፡- ሥርዓተ ክህነትን የሠራቸው (ሐ) ተጠቃሾች ናቸው።

የቀኖና ጠቀሜታ

  • መናፍቃንና ኑፋቄዎች ይለዩበታል።
  • የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሥርዓት እንዲኖር ያደርጋል።
  • የቤተ ክርስቲያን አንድነት ይጠበቃል (ዮሐ. 15፥1–29፣ ሐዋ. 15፥1-29)።
  • በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን የኾነውን የቤተ ክርስቲያን ካልኾነው መለኪያ (Standard) በመኾን ያገለግላል፡፡
ትውፊት (Tradition)

አወፈየ” ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ውርስ፥ ቅብብል ማለት ነው፡፡ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ውርስ ማለት ነው (1ቆሮ. 15፥3፣ 1ቆሮ. 4፥7)።

ትውፊት በግሪክ “ፓራላምባኖ” (Paralambano) ተብሎ ይጠራል፤ ትርጉሙም “መቀባበል ወይም መውሰድ” ማለት ነው፡፡ በዕብራይስጥ ከግሪኩ ጋር የሚስማሙ ወይም ተመሳሳይ የኾነ ትርጉም ሲኖራቸው “ማሳር” እና “ኪውቤል” የተባሉ ኹለት ቃላት ጥምረት ሲኾን፤ ማሳር ማለት ማቀበል ወይም ማውረስ ሲኾን ኪውቤል ማለት ደግሞ መቀበል ማለት ነው፡፡

በሌላ አገላለጽ ትውፊት ሲባል ከመለኮት ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠትን ሃይማኖት እና መንፈሳዊ ውርሶችን እንደነበሩ ጠብቃ ለማቆየት እስከ ደም ጠብታ ድረስ ታግሎ በመጠበቅ ማስተላለፍን ያመለክታል (ይሁዳ ቁ. 3)።

ትውፊትን በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ልንከፍላቸው እንችላለን፡-

  1. ቁሳዊ፡- አብያተ ክርስቲያናት፥ ንዋየ ቅድሳትን፥ መጽሐፍትን እና የመሳሰሉትን።
  2. ቃላዊ፡- ትምህርቶችንና መልዕክቶችን።
  3. ርእያዊ፡- በማየትና በመስማት የተወረሰውን ያመለክታል፡፡

የሃይማኖት ጥቅም ምንድን ነው?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *