Divine Liturgy Service Hours: Saturday @ 5:00 am – 8:00 am | Sunday @ 4:00 am – 7:00 am

ሀልዎተ እግዚአብሔር

የማይታይና የማይመረመር ኹሉን ማድረግ የሚችል፥ ኹሉን የፈጠረ፥ የመዠመሪያ ያልነበረው መጨረሻም የማይኖረው፥ ለዘላለም የሚኖር አንድ አምላክ መኖሩን ማመን ለሰው ልጆች መሠረታዊ ነገር ነው፡፡

ሀለወ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጉሙም መኖር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሀልዎተ እግዚአብሔር ማለት የእግዚአብሔር መኖር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ለዘመኑ የጊዜ ቀመር አይቀመርለትም፡፡ በዚህን ጊዜ ነበር በዚህኛው ጊዜ ደግሞ አልነበረም አይባልም፡፡ እግዚአብሔር ከዓለም (ከፍጥረት ኹሉ) አስቀድሞ መኖሩ ይታወቃል እንጂ የኖረበት ዘመን አይቆጠርም፡፡

“እነሆ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፡፡ አናውቀውምም፡፡ የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም፡፡” ኢዮ 36 ፥ 26

እግዚአብሔር ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው ” መዝ. 73 ፥ 12 ‚እግዚአብሔር ከጊዛ ውጪ ነው “
በክርስትና ሕግ የእግዚአብሔርን መኖር ለማወቅ እና ለመረዳት ቍልፍ እምነት ነው፡፡ ከእምነት ያልተነሣ ሰው በፍጹም ወደ እግዚአብሔር ሊደርስ አይቻለውም፡፡ ከእግዙአብሔር ጋር ላለን ግንኙነት ዋናው መሠረት እምነት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ እግዙአብሔርን የማወቅ መሠረቱ እምነት ስለኾነ ‚በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና ‛ 2ቆሮ. 5 ፥6 ተብሎአል፡፡ክርስትና ማየት ማመን ነወ በሚለው ብሒል አትመራም፡፡ጌታችንም ‚ሳያዩ የሚያምኑ ብፁአን ናቸው‛ ያለው እምነት መሠረት በመኾኑ ነው፡፡ ማቴ. 5 ፥ 1 ይኹን እንጂ እግዚአብሔር መኖር ለማወቅ መሠረቱ እምነት ቢኾንም ብቸኛው ግን አይድለም ፡፡ ፈጣሪን እናውቅ ዘንድ የሚያግዘንን ነገሮች ሰጥቶናል ፡፡ እንድናውቀው አጋዥ አድርጎ ከሰጠን ውስጥ ሥነ ፍጥረት ሕሊና ፣የሰው ልጅ የተፈጥሮ ዜንባሌ እና ቃለ እግዙአብሔር ዋናዎቹ ናቸው::

እግዚአብሔር አለ ከተባለ ለምን አይታይም?

እግዚአብሔር ባሕርይው የማይዳሰስ ረቂቅ ስለኾነ ባሕርዩ ለፉጡሩ አይታይም፤ ምክንያቱም ፉጡር ሊያየው የማይችል መንፈስ መለኮት ነውና። እንኳን ንጹሐ ሥጋ በሌለን በእኛ ሊታይ፥ ባለሟሉ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሊያየው ሽቶ የተሰጠው መልስ «ሰው ዐይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም» የሚል ነው (ዘጸ 33÷17-20, ዮሐ 4÷24)።


መለኮት መንፈስ ነው የሚታይ አይደለም፤ እግዚአብሔር በባሕርዩ ረቂቅ ነው፡፡ ስንል በርቀት ከእርሱ ጋር የሚወዳደረው የለም፤ ከማየት እንኳን ማየት ይርቃል፤ በምሳሌ ከአፈር ውሃ ይርቃል፥ ከውሃ አየር ይርቃል፥ እንዲሁም ከመላዕክትም ከአየርም ርቀት የእግዚአብሔር ርቀት ይበልጣል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በሰው አእምሮ አይመረመርም፡፡


ኹሉ ነገር የሚጨበጥና የሚዳሰስ ነው የሚለውን ሃሳብ ሙሉ በሙሉ እውነት ሊኾን አይችልም ከስነ ፍጥረት ሰው የማይጨብጣቸውና የማይዳስሳቸው መንፈሳዊ ባሕርይ ያላቸው ፉጡር መኖራቸው በቅዱስ መጻሕፍት ተረጋግጧል፡፡ የሚዳሰሰውን ፍጥርት በአእምሮ ጠባይ ተመራምሮ ማን እንዳስገኘ በምርምር ቀናቱ ካለ መረዳት ይቻላል ነገር ግን ዕውነትን ለማወቅ ፍቃደኝነቱ ከሌለ፥ ልቡናም በዕምቢተኝነት ጨለማ ከተጋረደ የጥበቡን ብርሃን ለማየት አይቻልም፡፡ ጥበብ ለማየት ፈጣሪ በሥነ ፍጥረት መርምሮ ሕልውናን መረዳት እርሱ በሚፈቅደው መንገድ ማምለክ ነውና፡፡ የማይታየው የማይዳሰሰው መለኮት በሥነ ፍጥረት ለፍጥረት እንደሚታወቅ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጽፎታል፡፡


« ዓለም ሳይፈጠር የማይታወቅ እግዚአብሔር በፍጥረቱ ይታወቃል በማሰብና በመመርመር አላወቅንም ብለው ምክንያት እንዳያገኙ ኃያሉና የ◊ለዓለም ጌትነቱ እንዲሁ ይታወቃል» ሮሜ 1÷20 «

የሚታየውንስ ተስፋ ማድረግ ተስፋ አይደለም የሚያየው ግን ማን ተስፋ ያደርጋል የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን » ሮሜ 8ቁ24

«ዓለሞች እግዚአብሔር ቃል እንደተዘጋጁ ስለዚኽም የሚታየውን ነገር ከማይታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን» ዕብ 11 ÷3 

በሥነ ፍጥረቱ ይታወቃል
  • «ራሱን ያለ ምስክር አልተወም» ሐዋ. 14 ፥ 17
  • «እያንዳንዱ ቤት በአንዱ ሰው ተዘጋጅቷልና ፣ ኹሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው፡፡» ዕብ. 3 ፥ 4
  • «ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ ፦ የሰማይ ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራሉ፡፡» መዝ. 18 ፥ 1
  • «እንስሶችን ጠየቅ ፣ ያስተምሩኽማል የሰማይ ወፎችን ጠይቅ ፣ይነግሩኽማል ወይም ለምድር ተናገር እርሷም ታስተምርሃለች ፣የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል ፡፡ እግዚአብሔር እጅ ይኽን እንዳደረገ» ኢዮ. 12 ፥ 7 – 9

ሥነ ፍጥረትን ማን ፈጠረው

ሥነ ፍጥረት ማለት የፍጥረት መበጀት ማለት ነው፡፡ ይኽ የሚታየው ዓለምና በውስጡ ያለው ኹሉ፥ ከዚህ የሚታየው ዓለም ውጭም ያለው የማይታየው ዓለምና በውስጡ ያሉት ረቂቃን ፍጥረታት ኹሉ በእግዚአብሔር ተፈጥረዋል፡፡
(ዘፍ 1÷1፣ መዝ 101- 25, ኢሳ 66÷1-2 ዕብ 11÷3)

እግዚአብሔር ግዘፍንና ረቂቁን ዓለም የፈጠረው ከምንም ተነሥቶ የሚያገናኛቸውና የሚያቀላቅላቸው ነገር ሳይኖረው /አም ኀበ አልቦ/ ነው፡፡ መዝ. 32፡9, 2መቃ, 14፡10, ጥበብ,11፡8, ሓዋ, 17፡24‹ ዕብ.11፡3, መዝ.143፡5

ሥነ-ፍጥረት በስንት ቀን ተፈጠሩ?

እግዚአብሔር ፍጥረታትን ፈጥሮ ያከናወነበት በስድስት ቀናት ውስጥ ነው (ዘፍ.1 እና 2, ዘጸ. 20፡9-11)። ፍጥረታት ኹሉ በ6 ቀናት ተፈጥሮ እንደ ተፈጸመ ኦሪት ዘፍጥረት ያስረዳል፡፡ በእነዚህ ቀናት የተፈጠሩት ፍጥረታት እያንዳንዳቸው ቢቆጠሩ ፍጡር ተናግሮ አይፈጽመውም ነበር፡፡ ነገር ግን በባሕርያቸውና በአኗኗራቸው በ22 ይመደባሉ (ኩፋ 3፡9, 2፡8)።

የሥነ-ፍጥረት አፈጣጠር ዓይነት

  1. ቀዳማይ ፍጥረት፡- በመጀመሪያ /እም ኀበ አልቦ ኀበቦ/ ካለ መኖር ወደ መኖር የተፈጠረው ፍጥረት ኁሉ ቀዳማይ ፍጥረት ይባላል፡፡ ለምሳሌ- ምድር ቀዳማዊያን ፍጥረታት ናቸው፡፡ በቃለ እግዚአብሔር እም ኀበ አልቦ መጡ እንጂ በራሱ ሃላዊነት ካልነበረ ግዘፍ ነገር አልተገኙምና፡፡
  2. ካልዕ ፍጥረት፡- ከግብር የተገኘው ግብር ኹሉ ካልዕ ፍጥረት ይባላል፡፡ ለምሳሌ ሰው፣ አራዊት፣ አዋፍና ወዘተ ካልዕን ፍጥረታት ናቸው፡፡ አስቀድሞ ከፈጠረው /ከተገኘው/ ከመሬት ተፈጥረዋልና፡፡ (ዘፍ. 2÷7)
ይኽን የፍጥረት ዓይነት በዝርዝር በሦስት ዓይነት መንገድ ይመደባሉ፡-
  • በአርምሞ /በዝምታ/፡- አራቱ ባሕርያተ ሥጋ፣ ጨለማ፣ መላዕክት፣ ሰማያት
  • በነቢብ /በመናገር/፡- ብርሃን፣ ጠፈር፣ እንስሳት፣ ዕፀዋት
  • በገቢር /በመሥራት/፡- ሰው ብቻ
በስድስቱ ቀናት የፍጠሩት ፍጥረታት (ዕለተ እሑድ)

እግዚአብሔር በመጀመሪያ ቀን ስምንት ፍጥረታት እም ኀበ አልቦ ኀበቦ /ካለመኖር ወደ መኖር/ አምጥቶ ፈጠራቸው፡፡ እነዙኽም፡- ነፋስ፣ እሳት፣ ዉሃ፣ አፈር /መሬት/ ሲኾኑ አራቱ ባሕርተ ሥጋ ይባላሉ፡፡ እንዲሁም ጨለማ፣ ሰማያት፣ መላዕክትና ብርሃን ናቸው፡፡ (ዘፍ.1÷1)

  • እሳት፡- እሳት የእግዚአብሔር ክብር ነው (ሕዝ.1፡4)፣ በምሳሌነት የእግዚአብሔርን ቅድስናና ቁጣ ያሳያል፡፡
  • ነፋስ፡- ነፋስ የእግዚአብሔር እስትንፋስም ይባላል።
  • ውሃ፡- ውሃ የእግዚአብሔር በረከት ነው (መዝ. 22፡2)።
  • አፈር / መሬት /፡- የእግዚአብሔር ባለጠግነቱን ያመለክታል፡፡
  • ጨለማ፡- የኦሪት (የብሉይ ኪዳን ዘመን) ምሳሌ ነው፡፡
  • ሰማያት፡- ከምድር በላይ ያለው ሰማያት /ሰማይ/ ይባላል፡፡ ሰማየ ሰማያት የምንላቸው ከላይ ወደ ታች፡- ፅርሀ አርያም፣ መንበረ መንግስት፣ ሰማይ ውዱድ፣ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፣ ኢዮር፣ ራማ እና ኤረር ናቸው።
  • መላእክት፡- መላዕክት ረቂቃን ናቸው፡፡ ሕያዋንና ዘላለማዊያን ሲኾኑ ጾታ የላቸውም፡፡ ነገር ግን በወንድ ጾታ ይጠራሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *