ቅዱስ ሚካኤል በጥንተ ተፈጥሮ በዕለተ እሑድ ከተፈጠሩት ፍጥረታት ከመላእክት ወገን አንዱ ሲሆን ኃያል መልአክ ነው።መላእክት በነገደ 10 ሲሆኑ ስመ ነገዳቸው አጋዕዝት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌል፣ ኃይላት፣ አርባብ፣ መናብርት፣ ሥልጣናት፣ ሊቃናት፣ መኳንንት፣ መላእክት ይሰኛል፡፡ቅዱስ ሚካኤል ከእነዚህ ውስጥ ኃይላት በተባሉት በኢዮር ውስጥ ከሚገኙ አራት ከተሞች በላይኛው ማለትም በአራተኛው ከተማ በሚኖሩት ነገደ መላእክት ላይ ተሹሟል። ሳጥናኤል በካደ ጊዜ ዲያብሎስን ከመላእክቶቹ ጋር ሆኖ ድል ስለነሳው አንድም ደግሞ እግዚአብሔር ባወቀ፤ በትህትናውና ደግነቱ በ99ኙ ነገደ መላእክት ላይ ሁሉ ተሹሙ ሊቀ መላእክት ተብሏል።
የስሙ ትርጓሜ
ሚካኤል የሚለው ስም አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተሰኘው መዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው እንደገለጹት የቃሉ መነሻ ዕብራይስጢ ሲሆን ሚ ማለት መኑ፤ ካ ማለት ከመ፤ ኤል ማለት ደግሞ አምላክ ማለት ነው። የ ስሙ ትርጓሜ መኑ ከመ እግዚአብሔር ወይም እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው? ማለት ነው፡፡
ይህም የእግዚአብሔርን ገናናነትና እሱን የሚመስል አምላክ እንደሌለ የሚያመለክት በአጠቃላይ እንደ እግዚአብሔር ያለ ቅዱስ፣ንጹሕ፣ ርኅሩኅ፣ ኃያል፣ ረቂቅ ማን አለ? እንደማለት ነው፡፡
ቅዱስ ሚካኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠውን የባለሟልነት ክብር የሚገልጹ የስሙ ዘርፍ ሆነው የሚጨመሩ መጠሪያዎች አሉት ። እነዚህም መልአከ ኃይል፣ መጋቤ ብሉይ፣ መልአከ ምክሩና እኒህን የመሠሉት ናቸው፡፡
- መልአከ ኃይል የተባለው እግዚአብሔር በእርሱ አማካኝነት ታላላቅ ሥራዎችን በመሥራት ኃይሉን ስለገለጸ ዲያብሎስን ከነሰራዊቱ ስላሸነፈ ነው።
- መጋቤ ብሉይ ያሰኘው ደግሞ በብሉይ ኪዳን ዉስጥ ከእግዚአብሔር እየተላከ ብዙ ታላላቅ ሥራዎችን የሠራ እንዲሁም በብሉይ ኪዳን በመከራ ለነበሩ ለቅዱሳን ሁሉ ሞገስ፣ ረዳትና አዳኝ ሲሆናቸው የነበረ በመሆኑ፣ ሕዝበ እስራኤልን ለ40 ዘመን በበረሃ የመራቸው እና ሲመግባቸው የነበረ በመሆኑ ነው።
- መልአከ ምክሩ ወይም የእግዚአብሔር የምክሩ አበጋዝ የተባለበት ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔርን በምክሩ ይረዳዋል ማለት ሳይሆን እግዚአብሔር የሚሠራውን ሥራ ለወዳጁ ለቅዱስ ሚካኤል ይገልጽለታል፤ በእርሱም አማካኝነት ይሠራል ለማለት ነው።
ቅዱስ ሚካኤል በመጽሐፍ ቅዱስ ዉስጥ
ቅዱስ ሚካኤል በ ብሉይ ኪዳን
- ኢያ 5፡13᎐14 ቅዱስ ሚካኤል ለኢያሱ ወልደ ነዌ በሰው አምሳል ተገልፆ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ አየ፤ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ ከ እኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ? አለው። እርሱም እኔ የእግዚአብሔር ሰራዊት አለቃ ሆኜ አሁን ወደ አንተ መጥቻለሁ አለ ኢያሱም ወደ ምድር በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደ።
- መዝ 33፡7 ዘወትርም ያድናቸው ዘንድ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሠፍራል።
- መዝ 90፡11 እግራችን እንዳይሰናከል ዘወትር ይጠብቀናል።
- መሳ 13፡18 የቅዱስ ሚካኤል ስሙ ድንቅ ነው።
- ዳን 10፡21 ከእርሱ በቀርስ የሚያጸና ማን አለና!።
- ዳን 12፡1 ለሕዝቡም የሚቆም ታዳጊ መልአክ ነው።
- ኢያ 5፡15 በፊቱ ሲቆምም ስለክብሩ ጫማ አዉልቆ፡ባጭር ታጥቆ ነው።
ቅዱስ ሚካኤል በሐዲስ ኪዳን
- ቅዱስ ሚካኤል በሐዲስ ኪዳንም እንደሚቀጥል ነቢዩ ዳንኤል በትንቢቱ እንዲህ በማለት ተናግሯል “በዚያ ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ ሚካኤል ይነሳል”። ዳን 12፡1
- ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በ እግዚአብሔርም መለከት ከሰማይም ይወርዳልልና በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሳሉ። 1ኛ ተሰ 4፡16
- የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከ ዲያቢሎስ ጋራ በተከራከረ ጊዜ ስለሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ጌታ ይገስጽህ አለው አንጅ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም፡፡ይሁዳ 9
- ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋራ ተዋጋ አልቻላቸውም። ራእይ 12፡7
የቅዱስ ሚካኤል በዓላት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓመቱ ውስጥ የሚከተሉትን ዕለታት ለመልአኩ መታሰቢያ አድርጋ አውጃቸዋለች። እነርሱም፦
- ኅዳር 12፡ የተሾመበት ዲያብሎስን ድል የነሳበት ህዝበ እስራኤልን የመራበት ዕለት
- ኅዳር 13፡ በዓለመ መላእክት ያሉ አእላፍ መላእክት በዓለ ሲመቱን ተሰብስበው ያከበሩበት ቀን ነው። ዕለቱም አእላፍ መላእክት ይባላል።
- ታኅሣስ 12፡ ዱራታወስና ሚስቱ ቲወብስታን የረዳበት ዕለት ነው።
- ጥር 12፡ የደሃዋን ልጅ ተላፊኖስን የረዳበት፣ ያዕቆብን ከወንድሙ ከኤሳው እጅ የጠበቀበት ዕለት ነው።
- የካቲት 12፡ የሚበላው የሚጠጣው የሚለብሰው ላጣ አንድ ሰው በሰው አምሳል ተገልጦ ከሀብታም ሲበደር ዋስ የሆነበት፣ ሶምሶንን ረድቶ አሕዛብን ያጠፋበት ዕለት ነው።
- መጋቢት 12፡ ማቴውስ የተባለውን ሰው እና ሚስቱን እንዲሁም ልጆቹን የረዳበት፣ የበለአምን አህያ ያናገረበት ዕለት ነው።
- ሚያዝያ 12፡ አዳምን ወደ ገነት ያስገባበት፣ ኤርምያስን ከእስር ቤት ያወጣበት ዕለት ነው።
- ግንቦት 12፡ ዳንኤል በአንበሳ ጉድጓድ ውስጥ ሳለ እንባቆምን ምግብ አስይዞ በአንዲት የራስ ጠጉሩ አንጠልጥሎ ከኢየሩሳሌም ዳንኤል ወዳለበት ወደ ባቢሎን ወስዶ ዳንኤልን በጉድጓዱ ውስጥ የመገበበት ዕለት ነው።
- ሰኔ12፡ ቅዱስ ሚካኤል እናታችን ቅድስት አፎምያን ከጠላት ዲያቢሎስ እጅ ያዳነበት እንዲሁም ባሕራንን ከባሕር ያወጣበት ዕለት ነው።
- ሐምሌ 12፡ የደሃይቱን ልጅ ተለሀሶንን ከባሕር አውጥቶ የጠበቀበት፣ ንጉሥ ሰናክሬምን ከነሠራዊቱ ደምስሶ ጻድቁ ሕዝቅያስን ያዳነበት ዕለት ነው።
- ነሐሴ 12፡ ሶስናን ከእደ ረበናት ያዳነበት፣ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስን ረድቶ መክስምያኖስን ድል ያደረገበት ዕለት ነው።
- ጳጉሜን 3፡ ቅዱስ ሩፋኤል ያሳረገው የዓመቱን ጸሎት ዕጣን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብበት ዕለት ነው።
- መስከረም 12፡ ሰማዕቱ ፋሲለደስን የረዳበት፣ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሡ ሕዝቅያስ ሂዶ እንዲመክረው ያደረገበት ዕለት ነው።
- ጥቅምት 12፡ ነቢዩ ሳሙኤል ዳዊትን ቀብቶ እንዲያነግሠው የላከበትና ዳዊትን የረዳበት ዕለት ነው።
በዚህ በዓላት ወደ ፈጣሪው 14 ልመናዎችን ያቀርባል። ቅዱስ ያሬድም፡
“ወአሰርቱ ወአርባዕቱ ትንብልናከ” በማለት የቅዱስ ሚካኤል ልመናዎች 14 እንደሆኑ ገልጿል።
14ቱ ልመናዎቹም በ 14ቱ በዓላቶቹ በጉልበቱ እየሰገደ ፈጣሪውን ለሰው ምሕረት ይቅርታ እንዲያደረግላቸው የሚለምናቸው ልመናዎች ናቸው። የመልአኩ አማላጅነት ሁላችንንም በእርሱ ያመን የመንፈስ ልጆቹን ይጥበቀን!